Loading...
 • Pixma

  የክርስቶስን ፍቅር ለዓለም ማካፈል!

  Sharing the love of Christ to the nation!

 • CONNECT WITH US
  AND
  KEEP IN TOUCH
  Nilesat and utelsat Satellite
  Rocu TV
  Internet TV
  Social Network
  iMac Responsive
  iPad Responsive
  iPhone Responsive

Watch Elshaddai Television Live!/ ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ይመልከቱ!

 

iPhone5c

ፓስተር ገነነ ወልደሰማያት  ትውልድ ለክርስቶስ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ደቡብ አፍሪካ /የክብር ወንጌል ቲቪ/

አስቀድሜ ስለ ኤልሻዳይ ቴሌቪዝን ኔትወርክ፣ ስለ ፓስተር አበራና ፓስተር በለጡ፣ በዚህ ራእይም ተሰማርተው ስላሉና በኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔት ወርክ እየተሰራ ስላለው ስራ የስራው ሁሉ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ላመሰግን እወዳለሁ። በመቀጠል ራእዩን ከእግዚአብሔር ተቀብለው በታማኝነትና በትጋት ይህን ራዕይ ለማስፈጸም ራሳቸውን ሁለንተናቸውን የሰጡትን ፓስተር አበራንና ፓስተር በለጡን አመሰግናለሁ። በትናንሽ አዳራሾች ይሁን በትላልቅ አዳራሾች በስቱዲዮዎችም የሚካሄዱ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች በዓለም ዙሪያ ተበትነው ላሉ ወገኖቻችን ሁሉ በረከቱና ጸጋው ይደርሳቸው ዘንድ ምክንያት ስለሆኑ፤ ፈር ቀዳጅም ስለሆኑ ታሪክ የማይረሳቸው ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው ላመሰግናቸው የወደድኩት። ከቴሌቪዥኑ ኔት ወርክ ባለፈ ደቡብ አፍሪካ አምና በ2013 በመጡ ጊዜ አብረን ለማሳለፍ ዕድል አግኝተን ስለነበር ለቅዱሳን ያላቸውን ፍቅር፣ ወንጌል እንዲሮጥ ያላቸውን እውነተኛ ቅንአት፣ አገልጋዮች እንዲወጡና ለብዙሃን በረከት ምክንያት እንዲሆኑ ያላቸውን ልበ ሰፊነት አይቻለሁ። እግዚአብሔር አሁን እየተጠቀመባቸው ካለው በላይ በሰጣቸው ራእይ እንዲሰፉና ለብዙዎች በረከት እንዲሆኑ ጸጋው በእነርሱ ላይ እንዲበዛ የእኔና የቤተክርስቲያናችን ጸሎት ነው።

“የክብር ወንጌል ቲቪ” የሚለው ፕሮግራማችንን በኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔት ወርክ ማስተላለፍ የጀመርነው ከ ፌብርዋሪ 2013(እ. ኢ. አ.) ጀምሮ ሲሆን ዓላማችንም እግዚአብሔር በከፈተው በዚህ በር (ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትወርክ) የወንጌልን ምሥጢር በመግለጥ ላመኑት መታነጽ፤ ላላመኑት ደግሞ መዳን እንዲሆን በማሰብ ነው። በዚህ አንድ ዓመት ከግማሽ ጊዜ ያህል ውስጥ ብዙ ምስክርነቶችን በስልክ፣ በኢሜይል፣ በቫይበር፣ በዋትስ አፕና በአካል ደርሰውናል። ለሰዎች በረከት ምክንያት ከመሆን የሚልጥ ምን እርካታና ደስታ አለ? የእግዚአብሔርን ሚስጥር እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን በመግለጥ ሰዎች ታንጸው ከማየት የሚበልጥ ምን እሰይ የሚያሰኝ ነገር አለ? ከምንጠብቀውና ክምናስበው በላይ እግዚአብሔር እየሰራና እያደረገ ስላለ እግዚአብሔርን እጅጉን እናመሰግናለን። በዚህ ሁሉ ሕዝባችን ምን ያህል እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ነገር የተራበና የተጠማ እንደሆነ ይበልጥኑ ማየት ችለናል። ያለብንን ይህን የተራበውንና የተጠማውን ሕዝብ የማገልገል ዕዳ በይበልጥ ተረድተናል። እግዚአብሔርም በሚያበዛልን ጸጋ ሁሉ በደስታና በፍቅር ሕዝባችንን እናገለግላለን።

SOME OF OUR PROGRAMS

ቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና / REV. DR. TOLLOSA GUDINA

የኢትዮጵያ ኢቫንጀሊካን ቤተ-ክርስቲያን አትላንታ ጆርጂያ / Ethiopian Evangelical Church: Atlanta, Georgia

ፓስተር ዘሩባቤል ቤተመንግስቱ / Pastor Zerubabel BeteMengistu

ቤዛ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪ / Beza international Minstries

ፓስተር ገነነ ማስረሻ / PASTOR GENENE MASRESHA

የክብር ወንጌል

የቴሌቪዥን አገልግሎት

ፓስተር ፒተር ማርዲግ / PASTOR PITER MARDING

የህያው ክርስቶስ አለማቀፍ ቤተክርስቲያን: Living Christ Church International

ከበደ መርጊያ እና አስቴር ሳቡሬ/ KEBEDE MERGIYA AND ASTER SABURE

የመዳን ቀን የቴሌቪዥን አገልግሎት: THE DAY OF SALIVATION

ተስፋ ትውልድ የልጆች ፕሮግራም / HOPE GENERATION

የልጆች ዕድገት ሥልጠናና ምርምር ማዕከል እየተዘጋጀ በኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትወርክ የሚቀርብ

ከአገልጋዮች አንደበት

መጋቢ ሮማን ኃ/የሱስ ሰሊሆም ዓለም አቀፍ የምሥራቹ ወንጌል አገልግሎት

በዚህ አገልግሎት ብዙ ድንቆች እየሆኑ በርካታ ምስክርነቶች ደርሰውናል:: ከሁሉ ድንቅና ድንቅ እንዳገልጋይ ነፍሳት ሲድኑ ማየት ነው:: ከብዙዎቹ ለምሳሌ በነበረችበት ሃይማኖት “ቁርአን መቅራትና ዱአ በማድረግ” ታገለግል የነበረች ባለችበት በአረብ ምድር ሆና የቴሌቪዥን ቻናል ስትቀያይር ባላሰበችው ሁኔታ ባገሯ ቛንቛ የሚተላለፍ ፕሮግራም ስታይ ተደስታ በሰማችው ተማርካ ለአምስት ጊዜ ጌታ ኢየሱስን በመቀበል ስትፅልይ ቆይታ የበለጠ ለመረዳትና ለጸሎት ደውላ ጌታን የግል አዳኟ አድርጋ በመቀበል ዛሬ ከሌሎች ጋር በስልክ የደህንነት ትምህርት በመማር ላይ ነች:: ሌላይቱ እህት ሃይማኖቴ ከእናንተ ይለያል፡ ፡ ግን ብዙ ግዜ በቴሌቪዥን ፕሮግራማችሁን ተከታተልኩኝ፡፡ አሁን ግን ልወስን ግድ ስለሆነብኝ የምትይኝን ልሁን ብዬ ደወልኩልሽ፡ ፡ አለችኝ እኔም ስለጌታ አዳኝነት በመንገር ጌታን እንድትቀበል ከጸለይኩና ከመከርዃት በኋላ ስልኩን ዘግታ ከተሰነባበትን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግማ ደወለችልኝ ምክንያቷን ስጠይቃት ወንድሜ ብቻሽን ለምን ጌታን ተቀበልሽ ብሎ ተቆጣኝ፡፡ ለሱም እንድትጸልይለት ፈልጎ ነው ብላ ሁለቱም ባንድ ቀን ጌታን ተቀብለዋል፡፡ በተለይ በአረቡ ምድር በስደት ያሉ ወገኖቻችን የጌታን ቃል በመስማት እየዳኑ ስለሆነ ክብር ለእርሱ ለጌታችን ይሁን:: በዚሁ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት አንዷ በልጅነቷ ስትጫወት አይኗ በእንጨት ተውግቶ ጠፍቶ የነበረች ሴት አስራ ሁለት አመት ደም ይፈሳት የነበረች ሴት ጨርቁን በእምነት በመንካት እንደተፈወሰች ስትሰማ ለኔም ዛሬ ይሄ ፈውስ ይሁንልኝ ብዬ ቴሌቭዥኑን ስዳስስ ፈውስ ሆነልኝ ብላ ደውላ መሰክረችልኝ:: ይህ እግዚአብሔር ከአገልግሎቱ ጋር አብሮ መሆኑን የሚያሳይና አብዝተን እንድንዘረጋ የሚያበረታታ ነው:: በሆነው ሁሉ የስራው ባለቤት ታላቁ ጌታ ይክበር::

ሬቨረንድ ሂርጶ ኩምቢ: የአማኑኤል ክርስትያን ህብረት መጋቢ/ ዩኬ/

ፓስተር አበራ ሀብቴን ያገኘሁት በእንግሊዝ ሀገር ከሎንዶን ከተማ ውጭ ባሉት በሊድስና በሼፊልድ ከተሞች ለቤተ ክርስትያን ተከላና ለወንጌል ስርጭት ይንቀሳቀስ በነበረበት ግዜ ሲሆን ለረዥም ግዜ አውቀዋለሁ፡፡ ታዲያ ከአስር ዓመት በፊት በ2004 ዓ.ም /እ.ኤ.አ/ የክርስትያን መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ስርጭት ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ሊጀምር እንደሆነ ሲነግረኝ በጣም ነበር የተደነቅሁት፡፡ ምክንያቱም በዚያን ግዜ እንደዚህ አይነት ነገር ይታሰባል ብዬ ስለማልጠብቕ ነው፡፡ ከተጀመረ በኋላ አገልግሎቱ ውጤታማ እንደሚሆን ጠብቔ የነበረ ቢሆንም በተለይ የገጠሩ ኅብረተሰባችን በዚህ ኣጭር ጊዜ ውስጥ የኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን በስፋት ተጠቃሚ መሆኑ ከጠበቅሁት በላይ ነውና በጣም አስገርሞኛል። ባለ ራዕዮቹ በዚህ ሰባት አመት ውስጥ አስቸጋሪ መንገዶችን ተጉዘዋል፡፡ አገልግሎቱ ያለ ምንም ኤደን ሀይሉ የገንዝብ ድጋፍ ስለ ተጀመረና ማንም በገንዘብ የሚረዳቸው ስላልነበረ ብዙ ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ ተገደዋል፡፡ የአየር ሰዓት ገዝተው የሚጠቀሙባቸው የቻናል ባለቤቶች ለክፍያ ሲያስጨንቁኣቸው በብድር አገልግሎቱን ለማስቀጠል ሞክረዋል፡፡አንዳንድ ግዜ እኔ ተጋባዥ አገልጋይ ሆኜ እዛው ቁጭ ብዬ በጣም አርፍደው ኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ከተኙ በኋላ ይሰጧቸዋል፤ አንዳንድ ግዜ ደግሞ ሳይጨርሱ ያስወጧቸዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ሆነው አገልግሎቱ እንዳይቆም በማለት 10.000 (አስር ሺህ) ፓውንድ ተበድረው እየሰሩ እያሉ የአንድ ቻናል ባለቤት የተሻለ አገልግሎት እሰጣችኋለሁ ብሎ ገንዘብ ካስከፈላቸው በኋላ ገንዘቡን ይዞ ተሰወረባቸው፡፡ ያን ጊዜ ልባቸው እጅግ ተሰብሮ ስለነበር በእኔ እይታ አገልግሎቱን ሊያቆሙ የሚገደዱበት ፈታኝ ጊዜ ነበር። ነገር ግን በእግዚአብሔር ልባቸውን አበርትተው ስለተራመዱ በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፈው ዛሬ ኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትወርክ በሁለት የማሰራጫ ጣቢያዎች የአፍሪካ፤ የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ ተመልካቾችን መድረስ ችሏል፡፡ እንዳው በዚህ አገልግሎት ከማይረሱኝ ነገሮች አንዱ ሶፋ ላይ ተቀምጠው ሲያገለግሉ አይቼ የእኔ አእምሮ የለመደው አገልጋይ ቆሞ ሲያገለግል ስለሆነ ሶፋ ላይ መቀመጣቸው ኣልተመቼኝም ነበርና ኣይ…ይ ኣልኩኝ። ከ 4 ዓመት በኋላ በኤልሻዳይ ቴሌቪዥን አገልግሎት ተጋብዤ ስሄድ ያቺው ያየሁዋት ሶፋ ላይ ሲያስቀምጡኝ አገልግሎቴን በንስሃ ጀመርኩኝ። ከዚያ በኋላ እየተመላላስኩ እንደ ተለመደው ሶፋ ላይ ተቀምጠን ስናገለግል አንድ ቀን ጌታ ኣንዲትን ሴት ፈውሷት የሰማሁት ምስክርነት ከትዝታዎቼ አንዱ ነው። ስለዚህ ሁሉ እርዳታው እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን

ሽመልስ ገሰሰ: የባህር ዳር ነዋሪ

ኤልሻዳይ ቴሌቪዥንን በጣም በጣም ተጠቅመንበታል፡፡ ኘሮግራሙ እንደ የደረጃው፣ እንደ የእድሜው፣ የህፃናትም፣ የአዋቂዎችም አለ፡፡ ወጣቶችን የሚመለከት፣ ለባለትዳሮች ጋብቻን በተመለከተ፣ የእህቶችም ኘሮግራም የሚስቶች ድርሻ የባሎች ድርሻ ምን እንደሆነ ይቀርባል፡፡ በጣም ከፍተኛ መታነፅና አስተዋፅኦ ነው እያደረገ ያለው፡፡

ለመንፈሳዊ ሕይወታችን በተለይ ደግሞ በአገልግሎት ዙሪያ ለምንሮጥና የውጭውን እናገለግላለን እያልን በልጆቻችን በኩል አልፎ የመሰጠት ሁኔታ እንዳይኖር፤ በዘመኑ ክፋት እንዳይወሰዱ፤ በዘመናዊነቱ ተስበው ልጆቻችን ወደ ሌላ ሌላ ነገር እንዳይሄዱብን እግዚአብሔር እንደ መሣሪያ እየተጠቀመበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የማያምኑ ሰዎች እንኳን እቤታችን ሲመጡ በጥሞና ነው የሚመለከቱት፣ እሁን እንደውም የማያምኑ ቤተሰቦቻችን ቤት ኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኘሮግራም አለ፡፡

ይኼም ነገር ሁልግዜ መነጋገሪያችን ነው፣ ልጆቻችንም እከሊትን እንኳ ኤልሻዳይ ስትከታተል አገኘኋት ይሉናል፡፡ ያው ለእኛ የተሸነፋ ላለመምሰል ነው የማይነግሩን፤ ነገር ግን እቤታቸው በጓዳቸው ኤልሻዳይን መመልከታቸው ለእኛ የፀሎታችን መልስ ነው፡፡ ይኸም ደግሞ እግዚአብሔር ምርኮ አድርጎ እንደሚሰጠን ለነገ ለተነገ ወዲያው ትልቅ ተስፋ ነው ፡፡ በአፋቸው ይቃወሙናል፣ እኛ አክራሪ ነን ይሉናል፤ እቤታቸው ግን ኤልሻዳይ ቴሌቪዥንን ያያሉ፡፡ ይኼ ሁሉ ስናየው ለእኛ ተአምር ነው፡፡” .

ሃዋርያ ዘላለም ጌታቸው: የተልዕኮ ለትውልድ ቤተ ክርስትያን መስራችና መሪ

አገልግሎት ራሱ ተፈጥሮው በአንድ አለም ውስጥ ሌላ ሌላ አለምን መግለጥ ነው፡፡ ፍጥረታዊ በሆነና በክፉ በተያዘ አለም ላይ ጽድቅና ብርሀን የተሞላ አለምን ለመግለጽ ስትነሳ የሚፈጠር የሁለት አለማት ግጭት ነው፤ በባለ ራዕይ መስክ ላይ የሚፈጠረው፡ ፡ ስለዚህ በማንኛውም የአገልግሎት መስክ ተግዳሮት አለ፡፡ ኤል ሻዳይ ቴሌቪዥንን ለየት የሚያደርገው ምንድነው እኛ ሀገር ሚዲያውን ለወንጌል ስራ መጠቀም ከኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን በፊት በሀሳብ ደረጃ እንጂ አልተለመደም፡ ፡ የነበሩት ሬዲዮዎቹም በቀደምት ቤተ ክርስትያናት የተያዙ ስለ ነበሩ ሚዲያው እነኛን አብያተ ክርስትያናትን መጋቢ ሆኖ የመጣው፡ ፡ እንደዚህ ግን ሚኒስትሪዬ ቴሌቪዥን ሚኒስትሪ ነው ብሎ የመጣ የለም፡፡ ሚዲያው ራሱን ችሎ እንደ ሚኒስትሪ ለማገልገል ሲወጣ ኤል ሻዳይ የመጀመሪያው ነው፤ ስለዚህ ቀዳሚ ያደርጋቸዋል፡፡

ሁሌም ደግሞ ቀዳሚ ሆነህ ስትወጣ ማህበረ-ሰቡ ውስጥ የተለየ አመለካከት አለ፡፡ እና የተወሰኑ ሰዎች እንደ አገልግሎት ሳይሆን እንደ ቢዝነስ ነው ያዩት፡፡ ይሄ ለነሱ ተግዳሮት ይመስለኛል፤ ምክንያቱም የአየር ስዓቱን ገዝተው ስለሚያገለግሉ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ አቅጣጫ ሲንቀሳቀሱ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ሌላው ማህበረ- ሰቡ ከቤተ ክርስትያን ውጭ ላለ የክርስቶስ አካል ያለው አመለካከት እንደ እግዚአብሔር መንግስት አመለካከት ሁሉንም ቤተ ክርስትያናት ያማከለ ሆኖ አልተቃኘምና እሱም ሌላው ተግዳሮት ነበር፡፡ ነገር ግን ሚዲያው ሁሉንም ክርስትያን እና ክርስትያን ያልሆነውንም የሚደርስ ነው፡፡

ፓስተር ሚካኤል ወንድሙ: የተቀባ የእግዚአብሔር ቃል ቤተ ክርስትያን መጋቢ

እኔ ወደዚህ ሚዲያ የመጣሁበት የራሴ አላማ አለኝ፡፡ የተቀባ የእግዚአብሔር ቃል ቤተ ክርስቲያን አሁን አስራ አምስት አመት ሆኗታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አንዳንድ የገጠሟት ተግዳሮቶች አሉ። ተግዳሮቶቹ ከሀገር ውስጥ አልፈው አለም አቀፍ መልክ የያዙበት ሁኔታም ነበረ፡፡ ስለ እኛ ጥሩ ያልሆኑ ወሬዎች ብዙ መሪዎች ጋር የደረሰበትና፤ ብዙ ሰዎች ስለ እኛ መጥፎ አመለካከት የያዙበት ወቅት ነበር፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማስተካከልና ይህች ቤተ ክርስትያን ምን እየሰራች ነው ? አስተምህሮዋስ ምንድነው የሚለውን ለነኚ ሰዎች ለመግለጽ ይሄ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉ ሰው ወደ አንተ አይመጣም፡፡ ወደ አንተ የሚመጣው ውስን ሕዝብ ነው፡፡ በሚዲያው ግን አንተ ወደ ሁሉ ሰው መሄድ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ወደ አሜሪካም፤ አውሮፓም፤ ክልሎችም ለመሔድ ይሄ ምርጡ መንገድ ነው ብለን አምነን፤ ሕዝቡ ስለኛ በወሬ የሰማቸውን ነገሮች ለምን ከኛ አይሰማቸውም ራሳችን የማናምንበት ነገር ካለ ለምን እንደማናምንበት የምናምንበትንም ለምን እንደምናምንበት ራሳችን ልንነግረውና ከዛ ሕዝቡ ሰምቶ ሊዳኘን ይገባል ብለን ወስነን ነው ወደዚህ ሚዲያ የመጣነው፡፡ ይሄ ከሌሎች ቤተ ክርስትያናትም ይለየናል ብዬ አስባለሁ፡፡

በዛ ጊዜ ፓስተር አበራ ወደ እኛ ቢሮ መጥቶ በዚህ በሚዲያ ዙሪያ ተነጋግረን ነበርና የነሱን መመዘኛ ስለማላውቅ ምናልባት እኛን ላያሳትፉን ይችላሉ የሚል የግል እሳቤም ነበረኝ፡፡ ከነበረው በፊት ከተወራው ወሬ የተነሳ፡፡ በኋላ ግን እሱን ሳየው እንደዚህ አይነት ነገር እሱ ጋ አልነበረምና መሳተፍ እንደምንችል ነገረኝ፡፡ በዚህ መንገድ ነው ወደ ኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን አገልግሎት የገባነው፡፡ የሚገርምህ በዚህ እድል መግለጥ የምፈልገው ነገር መቶ ፐርሰንት ሊባል በሚችል ሁኔታ ሰዎች ተቀየሩ፡፡ አላማችንን አሳካን፤ ብዙ ሰዉ የኛን አስተምህሮ የኛን እምነት አወቀ፡፡ ማን እንደሆንን ተረዱ፤ እምነታችን ወንጌላውያን እንደሆንን ተረዱ፡፡ እንዳውም በጣም ብዙ የአገልግሎት በሮች ተከፈቱ፡፡

ከሌላው የክርስቶስ አካል ጋር ያለን ህብረት ተጠናከረ፡ ፡ ዛሬ እውነቴን ነው የምነግርህ እግዚአብሔር እንዳገለግል የከፈተውን በር ብዛቱን ልነግርህ አልችልም፡፡ በጣም ብዙ ቤተ ክርስትያናት ውስጥ አገለግላለሁ፡፡ ከዛ ከነበረው ወጀብ የተነሳ ለራሴ የነገርኩት ነገር ነበረኝ፡፡ በቃ እዚ ብቻ ነው ማገልገል ያለብህ ፓስተር ሚኪ ሌላ ነገር አትመኝ ሌላው ያንተ አይደለም ብዬ ለራሴ ነግሬው ነበር፡፡ እናም ለረዥም አመት እዚችው አጥቢያ ላይ ነው ያገለገልኩት፤ ወዴትም ሳልወጣ፡፡ አልፎ አልፎ የምወጣባቸው በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ነበሩ፤ አሁን ግን ይሄ ተቀይሮአል፡፡ ለምሳሌ በሚቀጥለው ሳምንት ሙሉውን ሳምንት የተለያዩ ቤተ ክርስትያናት ላይ አገልግሎት አለኝ፡፡ ስለዚህ ለኛ ትልቅ ስኬት ሆኖልናል።

ፓሰተር አመሉ ጌታ: የቦሌ አማኑኤል ቤተ ክርስትያን ዋና መጋቢ

ቦሌ አማኑኤል ኤል ሻዳይ በጀመረ በስድስት ወር አካባቢ ነው ወደ ቴሌቪዥን አገልግሎቱ የገባነው፤ ከዚህም ባሻገር እንደ ቤተ ሰብ ሆነን የኤል ሻዳይን አገልግሎት በሀገር ውስጥ በማስተባበር በግሌም ጥረት እያደረግሁ ነው ያለሁት፡፡ ስንጀምር የጀመርነው አሁን ያገኘነውን ውጤት ጠብቀን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በድንቅ በከፈተልን በር ነው የገባነው፡፡ ባለፉት ስድስት አመታት በዚህ ቴሌቪዥን ስርጭት በሰራነው ስራ በአጥቢያ አገልግሎት የዛሬ መቶ አመት ልንደርስ የማንችላቸውን ሰዎች ደርሰናል፡፡ ይህን ፕሮግራም በአንድ ግዜ እስከ ሁለት ሚሊየን የሚገመት ሰው ይመለከታል፤ ይህንን ቁጥር ስቴዲየም በምታደርገው ኮንፍረንስ አታገኘውም፡፡ ቤተ ክርስትያናችን በመላው አለም ለሚገኙ በርካታ ሰዎች ወንጌልን ማድረስ ችላለች፡፡ እኔም በግሌ እግዚአብሔር በውስጤ ያስቀመጠውን ጸጋ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከትውልድ ጋር ለመካፈል ዕድሉን አግኝቻለሁ፤ እንግዲህ ለቤተ ክርስትያናችን፤ ለኔም፤ አብሮኝ ለሚያገለግለው ለነቢይ ታምራትም ኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ስለ ሰጠን ዕድል እናመሰግናለን፡፡

እግዚአብሔር በቴሌቪዥን አገልግሎት ሰዎችን ነክቶ ሲፈወሱ ማየት ትልቅ ነገር ነው፡፡ አንድ ግዜ አንድ አባት ከክፍለ ሀገር ደውለው ልጄ ይኸው ቴሌቪዥኑን እንኳን ማየት አቅቶኛል ብለው ስጸልይላቸው በዛው ስልክ ውስጥ ልጄ አየሁኝ ቴሌቪዥኑን አየሁት አሉኝ፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ ለኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን ፈንድ ሬዝ እያደረግን አንዱ ጫት እየቃመ ይሰማ ነበርና ደውሎ “ በቃ እኔ ከዛሬ ጀምሮ ጫት አቆማለሁ ይኸው ነገ የምቅምበትን አምስት መቶ ብር እሰጣለሁ ብሎ ” አምጥቶ አስገባ፡፡ ሌላው ደግሞ እየዞረ ዲሽ የሚሰራ ነው ግን አማኝ አይደለም፡፡ እሱም ደውሎ ይኸው ዛሬ የሰራሁትን ሁለት መቶ ብር እሰጣለሁ አለ፡፡

ሃዋርያ ዳንኤል መኮንን: የወንጌል ብርሀን ቤተ ክርስትያን ዋና መጋቢ

መጀመሪያ ምን ያህል ተመልካች እንደሚኖረው እርግጠኛ ሃዋርያ ዳንኤል መኮንን የወንጌል ብርሀን ቤተ ክርስትያን ዋና መጋቢ አልነበርንም፤ ግን እንደሚለመድና ብዙ ሰዎች እንደሚያዩት እርግጠኛ ሆንን፡፡ ለምሳሌ እኔ በዚህ ጉባኤ በአንድ ግዜ የማገኘው ሰው ውስን ነው፡፡ ነገር ግን በቴሌቪዥን ሲተላለፍ በጣም ብዙ ሕዝብ ይከታተላል፡፡ እና መልዕክቱ ከዚህ ከተያዝንበት ከትንሽዋ አካባቢ ወጥቶ ወደ ውጭ መድረሱን ስናይ በጣም ነው የተደሰትነው፡፡ ከዚህ ሌላ የኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን አገልግሎት ገንዘብ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ለዚህ ማስረጃ እኔ ልሰጥ እችላለሁ፡፡ እዚህ ቤተ ክርስትያናችን ውስጣዊ ችግር ተፈጥሮ መክፈል ባልቻልንበት ግዜ ለረዥም ወራቶች የኛን ፕሮግራም ኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን በደስታ በነጻ ያስተላልፉልን ነበር፡፡ ያ ያስተማረኝ ምንድነው እነኚ ቅዱሳኖች አላማቸው እግዚአብሔርን ማገልገል እንደሆነ ነው የተረዳሁት፡፡ ስለዚህ እንዳሰብነው ውጤታማ ነው፡፡

ኛ የማንረሳው ግዜ ቅድም የጠቀስኩት ነው፡፡ አንድ ወቅት ላይ ቤተ ክርስትያናችን ትልቅ ፈተና ውስጥ በምታልፍበት ግዜ፤ ሰዎች ቤተ ክርስትያኗን አለች የለችም እያሉ በሚጠይቁበት ግዜ ኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን ግን የየእሁዱን መልዕክታችንን ሲያስተላልፍ አሁንም የእግዚአብሔር ስራ እንደተሰራና እንደሚሰራ ሕዝቡ ሊያውቅ ችሏል፡፡ ሌላው የምናገኛቸው ፊድ ባኮች ለሕይወታችን ብርታት ሆነውናል። ለባለ ራዕዮቹ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት አለኝ፡፡ ባገልጋይ ሕይወት ውስጥ ተስፋ መቁረጥ ስለሚመጣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያን የማይረሳ ትልቅ ነገር አድርገዋል ታሪክ አስመዝግበዋል። ይህም ለመጀመሪያ ግዜ የሳተላይት መንፈሳዊ አገልግሎት በአማርኛ በመጀመር አይናችንን ከፍተውልናል፡፡ ከዚህ በኋላ ሌሎች ጣቢያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን እነሱን የማየው ቀድመው ሮጠው ለብዙዎቻችን ተሰውሮ ነበረውን በር የከፈቱልን ፋና ወጊዎች ስለሆኑ በዚህ እግዚአብሄርን ማመስገን ይኖርባቸዋል፡፡

ፓስተር ቶማስ ምትኩ: የመጽሐፍ ቅዱስ ሰራዊት አለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን ዋና መጋቢ

ለኛ ይሄ ትልቅ ዜና ነው፤ ምክንያቱም ስንጠብቀው የነበረ ነው፡፡ እግዚአብሔር በተለያየ መልኩ ስለ ሳተላይት ቴሌቪዥን ሲናገረን ነበር። እኛም ደግሞ ድሪም ስናደርግ (ስናልም) ነበር። ሆኖም ከተለያዩ ነገሮች የተነሳ ሳይሆን ቆይቶ ነበርና ፓስተር አበራ መጥቶ ይሄ ፕሮግራም ሊጀመር እንደሆነ ሲነግረን በጣም ነው ደስ ያለን፡፡ ይሄ አንደኛ ጌታ የተናገረው፤ ሁለተኛ እኛም ስንጠብቀው የነበረ ነው፡፡ ምክንያቱም ያለንን የእግዚአብሔርን መንግስት የወንጌል ራዕይ በፍጥነትና በስፋት የምናሰራጭበት ስለሆነ በእግዚአብሔር ግዜ የመጣ የእግዚአብሔር መልስ ነውና

ብዙ ነገር አለ ሚዲያው ላይ ተደጋግሞ ከመቅረብ የተነሳ በብዙ ሰዎች ዘንድ በቅርበት የመታወቅ ነገር አለ። ይሄንን በመንገድ ላይ፤ ሆቴሎች ውስጥና የተለያየ ቦታ ታየዋለህ፡፡ ሰው አይቶህ ከሄደ በኋላ እየዞረ ያይሀል። ይሄ እንግዲህ ከመጠቀማቸው የተነሳ ባላቸው ፍቅር ነው። አንዳንዱም ደግሞ አክብሮቱን ለመግለጽ እላፊ /የማይገባ/ ክብር ያሳይሀል። ይሄ እንግዲህ የሚዲያው ውጤት ነው፡፡ስለዚህ ሚዲያው የሴሌቢሪቲ አይነት ስሜት እንዳይፈጥር አገልጋዩ ሊጠነቀቅ ይገባል። ምክንያቱም ሚዲያው ምስል ቀያሪ ነው። ሚዲያው በሚያሳይህ መንገድ ራስን መሳል ጥሩ አይደለም፡፡ በቃ እሱ መልዕክት ማቅረቢያ ነው፡፡ እኛ አገልጋዮች ነን፤ አገልጋይ ደግሞ ጌታ አይደለምና የሎሌነት መንፈስ ይዘን ብንቀጥል ሚዲያው የሚፈጥረውን ምስል ብንቆጣጠረው ጥሩ ነው፡፡

ሃዋሪያ ዳንኤል ጌታቸው: የህያው ተስፋ የተአምራት አገልግሎት መስራችና ባለ ራዕይ

እኔ የቴሌቪዥን ጣቢያ ራዕይ ነበረኝ እና ለኤልሻ ዳይ ቤተሰብም ስለሆንኩኝ እንተዋወቃለንና ፓስተር አበራ መጥቶ ልንጀምር ነው ብሎ ሲነግረኝ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ ምክንያቱም ልጆች ሆነን ወንጌል በቴሌቪዥን ይሰበካል እያልን እንጸልይ ስለነበር ለኛ የራዕይ መፈጸም (ፉል ፊልመንት) ነው የሆነን፡፡ በኔ እምነት ማንም ይስራው ማን መፈጸሙን ነው እጠብቅ የነበረውና በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ወደ ሚቀጥለው መንፈሳዊ ደረጃ አደገች ነውያልኩት፡፡

በመጀመሪያ ለሁሉም በዚህ ፕሮግራም ለሚሳተፉ መስመር የጠበቀና የተስተካከለ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ያግዛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቀላሉ ጸጋችን በምድር ላይ እንዲሄድ ያስችላል፤ ለምሳሌ የእኔን አገልግሎት ብናይ ድሮም አገለግላለሁ፡፡ ኤል ሻዳይ ቴሌቪዥን ከመጣ በኋላ ግን በፍጹም በማልገምተውና በማልጠብቀው ሁኔታ አገልግሎቴ ተስፋፍቷል፡፡ በዛች ተፈውሳችኋል በምትለው ክሊፕ እንኳን ከሀገር ሀገር በቀን ከ40 በላይ ምስክርነት እሰማለሁ፡፡ ተጠቀማችሁ ወይ ለሚለው መልሱ ምን ጥያቄ አለው ነው፡፡ ኤል ሻዳይ ባይኖር ማን ያውቀናል ?የክርስቶስን የማዳን ኃይል ከመግለጽ በላይስ ምን ጠቃሚ ነገር አለ፤ ስለዚህ በጣም ውጤታማ ነን፡፡

Whats New